ከንፈር ግን ምን አስቦ ነው?

ነቃች። ተወጥራ… ታፍና ነቃች። የመጣላት እንዳይጠፋት ብላ በቅንጥብጣቢዎቹ ቢጫ ተጣባቂ ወረቀቶች ጀርባ ላይ በዱልዱም ቆራጣ እርሳስ እየተክለፈለፈች ሞነጫጫረችው… ከወረቀቱ የፈሰሱ ሆህያት ማስደገፊያውን ክርታስ አረጠቡት… ገሚሶቹ ትራፊ ቃላት ንፋስ እንደገረፈው ገለባ ከየፈሰሱበት እየተንሳፈፉ ክፍሏን እንደሙት መንፈስ ወረሩት።

እሷ እቴ ማፍሰሱ እንጂ ማቆሩ ግድ አይሰጣትም። አቀርቅራ ሆሄ በሆሄ እያነባበረች… ፊደል በፊደል እየደረበች የፈለቃት እስኪደርቅ በጥድፊያ የዱልዱሙ እርሳስ ጥቁር ጠመኔ እንጨቱ ጉያ ውስጥ እስኪደበቅ ካንቆረቆረች በኋላ ራሱን እንደሳተ ሰው የኋሊት አልጋዋ ላይ ተፈንግላ በደመቀ ኩርፊያ የተነከረ እንቅልፏን ትለጥጥ ጀመር። የተደረቱት ቢለያዩ… የተነባበሩት ቢነጣጠሉ… የፃፈችው ከዚህ ብዙም አይርቅ…


ከንፈር ባርያ ነው። ጌቶቹ እርስ በርሱ የሚያጋጥሙት አራት ሆህያት [መ በ ጰ ወ ፐ ] ናቸው። ከባርያ ጋር ምን አመላለሰን? በጌቶቹ በኩል ልክ ልኩን እንነግረዋለን። እነሆ

ከንፈር እንደሰው ነው። ፆታ አለው። ፆታው ሁልጊዜ ወጥ ባይሆንም የርሷ ከንፈር ግን የላይኛዋ ሴት ናት። ታችኛው ወንድ ነው። አጥንት አልተሰጣጡምና የሚጣበቁት እኩል ነው። አይጠባበቁም። ተጣብቀን እንቅር ብለው ተፈጥሯቸውን አይስቱም። ተለያይተን እንቅር ብለው ልስላሴያቸውን አያደርቁም። እግዜራቸው ሆሄ ነው። ሆሄያቸው ሲፈቅድ ይጣበቃሉ። ሲረግብ ይላቀቃሉ። ሴቷ ሰማይ ወንዱ ምድር… የሚፈጥሩት ደግሞ ቃል ነው። ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።

‘መ’ ጌታቸው ነው። ትርጓሜው ደግሞ ሁለት ነው “መጣበቅ” እና “መላቀቅ”… እንደ ብስክሌት ፔዳል አንዱ ያላንዱ አይሰምርም። “መ” መጀመሪያ ነው፤ መጨረሻም ነው። መምጣትም ነው መሄድም ነው። መውደድም ነው መጥላትም ነው። መገኘትም ነው መጥፋትም ነው። ከገዛ ከንፈሯ ካልተማረች ከማን ልትማር ኖሯል?

እግዜር ከንፈርን አልፈጠረም። ጅማሮው ከዦሮ ግንድ እስከዦሮ ግንድ የተዘረጋ የስጋ ቁርበት በአንዳች ምላጭ ተቀረድዶ እንጂ ቅጥ ያለው መስኮት አልነበረም። ሊሰነግ እንደተዘጋጀ የቃርያ ደረት ተሰነጠቀ እንጂ አልተፈጠረም። ጉንጭን የፈጠረ አምላክ የፈጠረውን ጉንጭ ሲሸነትረው ፈጠራ ብለን ልንመዘግብ ነው? በፍጹም! በጥበባችን ተመራምረን የሸነቆርናቸውን የጆሮና የአፍንጫ ጌጥ ማንጠልጠያ ቀዳዶች መች ስም ሰጠናቸው?

ከንፈር ከመሰንጠቁ ቀድሞ ወፍራም ጉንጭ ነበር። ተሰንጥቆ ወንዴና ሴቴው ሲከፈል በፈጣሪው ጥበብ ያልተገረመ መላዕክ አልነበረም። አንድ ተራ መላዕክ ግን ከትትትት ብሎ አምላኩ ላይ ሳቀ። አምላክ አዳምን ዲዛይን ከሚያደርግበት የምርምር ቴብሉ ዞር አለና መነጽሩን በጣቶቹ ወደታች ጎተት አድርጎ መላዕኩን “whats are you laughing about?” አለው። መላዕኩ በሳቅ የተረጩ እንባዎቹን እየጠረገ “አሽቃብጦ አደሮች ሆነው ነውንጂ ጉንጭ ሰንጥቆ ፓተንት መጠየቅ ምን ይገርማል” አለው።

እግዜር ተናደደ። ለማሸማቀቅ ብሎ እስኪ ያንተን ጥበብ ና አሳየን አለ። መላዕኩ ፈንጠር ብሎ ተነሳና እነዛን መንትያ ስንጥቆች ፈለቀቃቸው። ፍጹም አንድ አይነት ነበሩ። በግራ እጁ የላይኛውን ስንጥቅ ሲዳብሰው የልብ ቅርጽ አናት የመሰለ ቅጥ አወጣ። የታችኛውን ጎተት አድርጎ የላይኛው ተጋጣሚ አደረገው። መላዕክቱ ሁሉ አዲሱ ፈጠራ ቢገርማቸውም ከእንጀራቸው በላይ አልነበረምና በሁካታና በጩኸት አምጸው ሰደቡት። እግዜርም መላዕኩን አመስግኖ ማደር ካልወደደልህ “ከንፈህ እደር’ ብሎ አባረረው። ከንፈር የመጣው ከመላኩ እርግማን ከ “ከንፈህ እደር ነው። መላኩ የሰራቸውን ሴቴና ወንዴ ከናፍርት ለማራራቅ ብሎ እግዜር ወሬን ፈጠረ። ሆህያትን ፈጠረ።

“በ”… ያ የተባረረ መላዕክ ደጋፊ ሆሄ ነው። በቻለው መጠን ከናፍርቱን ያጣብቃል። እግዜርና መላዕክቱ ሌላ ሆሄ እየወረወሩ ያላቅቃሉ!

ከንፈሯ የገነት በር ነው። ችግሩ መግቢያ ይሁን መውጫ አያስታውቅም። የሚገለባበጡ ሰይፍ የሆኑ ቃላት ታውቃለች። እንዳልገባ ነው እንዳልወጣ? ሁለቱ የጥርሶቿ መጋረጃ ስጋዎቿ የተሰጣቸው ሞገስና ክብር ሲገርም! እስትንፋሷ ታምኖ ለከንፈሯና ለአፍንጫዋ ቀዳዶች ተሰጠ። ምግብና መጠጥ ያለከናፍርቷ ፍቃድ አያልፍም። ፊደሎቿ ቃል… ቃሎቿ ትርጉም የሚኖራቸው በከናፍርቷ ነው። ይሄ ሁሉ ከበቂቂቂቂቂ በላይ ነው።

እዚህ ሁሉ ላይ መሳምን ምን አመጣው? እስትንፋስ ላይ መሾም አንሶ ደግሞ ስሜት ላይ?… እህል ውሃ ላይ መንገስ አንሶ ደግሞ ሙቀት ላይ?… አንደበት ላይ አቃቤ መሆን አንሶ ደግሞ ፍቅር ላይ? ምን ጉድ ነው? እግዚዖ!

ምን ጉድ ነው? የላይ ከንፈሯ የታችኛው ልስልስ ዳሰሳ መቼ በቃውና… የታችኛው የላይኛው እርጥብ ሙቀት መቼ አጠረቃውና ነው ደግሞ ሌላ ከንፈር የምትሻው? ከንፈሮቿ እርስበርስ መሰናኘታቸው በቅቷት… በከንፈሬ ደግሞ መጣች።
በመተንፈሷ ብቻም ሳይሆን በመተንፈሴ፥ በእህሏ በውሃዬ… በሆሄዋ በፊደሌ… አቃቢ ልትሆን ወዳለች።

“ጰ” የአራት ከናፍርት ውህደትና ስማሬ ድምጽ ነው። የከንፈሯ ጣዝማ ያጣበቃቸው ከናፍርቴ ሲላቀቁ የምሰማው የመላዕክት ወረብ ወኪል ሆሄ።

ከንፈሯን ነገሩኝና ማንነቷን ደረስኩበት። ዞረች እንጂ “ወ” ራሷ ከንፈር ናት። ፊደሏን ማንበብ ችዬ ከንፈሯ ሊከብደኝ? በፍጹም። ሳጥናኤል ተገፍቶ ከሰማየ ሰማያት ሲጣል ያረፈው አፈር ላይ አልነበር? እየዳኸ አፈር መስሎ አደፈጠ። አምላክ ሁሉን ያውቃልና አዳምን ያበጀው ሳጥናኤል ካልዳኸበት ንጹህ አፈር ነበር። ግን አለ አይደል? አለቃ ሲጠነቀቅ ሰራተኞቹ ግድ የማይሰጣቸው የሚሆኑት ነገር? ሰው በተፈጠረበት በአርብ ማታ ክንፌን እያውረገረኩ እጨፍራለሁ ያለ መላዕክ ኢዮር በር ላይ የምሽት ተረኛ ጠባቂ መላዕክ መሆኑን አነበበ። ደበረው። እዛ ስንቷ ክንፋም እየጠበቀችው እሱ አለቃው ከዐፈር የጠፈጠፈውን አሻንጉሊት መጠበቁ አበሳጨው።

እየተማረረ የጭቃውን አሻንጉሊት ሲጠብቅ በጨረፍታ ዐየው። የጭቃው ምስል አለቃው ቁጭ አለቃውን ይመስላል። ተገርሞ “እንዴ ኢጎ!” አለ። ይህንን አፈርማ ከፈጣሪው ባንድ ነገር ማላቅ አለብኝ አለ። ወደምድር ወርዶ ጥቂት ጭቃ ዘግኖ ተመለሰ። ተመልሶ አድቦለቦለና ከአፍንጫው በታች ከአገጩ በላይ አሳምሮ መረገው። ለካንስ ምድር ወርዶ ያመጣ የመስለው ጭቃ ሳጥናኤልን ራሱን ነበር። አምላክ በነጋታው ቅዳሜ ረፍት ነው ብሎ ስራ አልገባምና… መላዕክት የጥበቃ ሽፍት ሲለዋወጡ ከንፈሩ አምልጦ ጠፋ። ሁሉን አወቁ አምላክ ይህን አላወቀም።

ያ ያመለጠው ከንፈር የርሷ መሆን አለበት። ስስማት እግዜር ይቀልብኛል… መላዕክት ይኮስሱብኛል… ፍጥረት ይሸክከኛል። የአምላክ ፍጡር ከምሆን ከእስትንፋሷና ከከንፈሯ ጣዝማ የተዋቀረውን የርሷን ወሬ ብሆን ይሻለኝ ነበር።

“ወ” ወይኔ! ነው… ወይኔ ወሬዋ በሆንኩ!

ፐ! እንዴት ትጥማለች?!

Create your website at WordPress.com
Get started